የኢትዮጵያ ገዳማት በኢየሩሳሌም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 1ኛ የዓለም አቀፍ የምዕመናን ጉባዔ

የኢትዮጵያ ገዳማት በኢየሩሳሌም
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 1ኛ የዓለም አቀፍ የምዕመናን ጉባዔ የቀረበ

ኅዳር 14 ቀን 1999

ከዳንኤል እስጢፋኖስ ዓለሙ
ኢየሩሳሌም

መግቢያ:

  በዓለም ታሪክ ሀገራችን ከምትታወቅባቸውና ከምትደነቅባቸው አንደኛው ታሪካችን በመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕ 10፡ 1-13 እንደተገለጸው ኢትዮጵያዊትዋ ንግሥተ ሳባ በጥበቡ ታዋቂነትና ተደናቂነት የነበረውን የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ለመመልከት ወደ ቅድስቲትዋ ከተማ ኢየሩሳሌም መምጣትዋ ነበር፡፡
ይኸው ታሪክ በክብረ ነገሥት ተጽፎ እንደሚገኘው ንግሥተ ሳባ ከንጉሥ ሰሎሞን ቀዳማዊ ምኒሊክን በመውለድዋ በ20 ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣቱ ለቀዳማዊ ምኒሊክ ክብር ይሆን ዘንድ እስራኤላውያን የበኩር ልጆቻቸውን ተከታይ ሆነውት እንዲሄዱ በማድረግ ለንጉሥ ሰሎሞን ክብርና ሞገስ ሁነው እንደታመኑት ለልጁ ምኒልክ ክብርና ሞገስ ይሆኑት ዘንድ እንዲከተሉት ማድረጉን ከአባቶቻችን የወረስነው ታሪክ ያስረዳናል፡፡
ይኸው ታሪክ በተጨማሪ እንደሚያስረዳን ለቀዳማዊ ምኒሊክ ረዳቱ እንድትሆን ታቦተ ጽዮንንም ይዞ ወደ ኢትዮጵያ መውሰዱ ነው፡፡ ንግሥተ ሳባም ወደ ኢየሩሳሌም የመጣትችበት ዘመን ከአባቶቻችን እንደተረmብነው ታሪክ ከንጉሥ ሰሎሞን ለእርስዋ እና ለተከታዮችዋ እንዲሁም ለዕቃ ማሳረፊያ ይሆናት ዘንድ ከንጉሥ ሰሎሞን የተሰጣት ቦታ ባሁኑ ዘመን የዴር ሱልጣን ገዳማችን በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ በሐዋርያት ሥራ ምዕ 8፡26–40 የኢትዮጵያ ጃንደረባ በሐዋሪያው ፊሊጶስ እጅ መጠመቁን በዚሁ ምዕራፍና ቁጥር እንረዳለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስረዳን ሌላ ኢትዮጵያውያን በቅድስት ሀገር ረጅምና የከበረ ቆይታ እንደነበራቸው ታሪክ ጸሀፊዎችና ጎብኞች የመዘገቡት ለመሆኑ ብዙ መረጃ እናገኛለን፡፡

ኢትዮጵያውያን በጥንታዊት ኢየሩሳሌም፡

በአራተኛው ክፍለ ዘመን የቅዱስ ጄሮም ደቀ መዛሙርት ቤተልሔም እያሉ በሮም ለሚገኙት ዘመዶቻቸው የግብዣ ደብዳቤ ሲልኩ “ከህንድ ከፋርስና ከኢትዮጵያ መነኮሳት እንዲሁም ተሳላሚዎች በየጊዜው ወደ ቅድስት ሀገር እንደሚመጡ” ገልጸዋል፡፡

እ.አ.አ በ786 ዓ.ም ጀርመናዊው ጳጳስ ቪሊቫልድ በገሊላ አንድ ኢትዮጵያዊ እንዳገኘ ገልጸዋል፡፡ ኢጣልያዊው የታሪክ ተመራማሪ ኢንሪኮ ቼሩሊ እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ እንደገመገመው በቅድስት ሀገር የሚገኘው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ከድኽነት የተነሣ ራሳቸውን ችለው የታዩበት ጊዜ አልነበረም፡፡
እ…አ በ1237 ዓ.ም. ሶርያዊው ታሪክ ጸሀፊ ባርህብሪዮስ አባ ቶማስ የተባሉ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኙ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ በወቅቱ በግብጻዊው ፓትርያርክና በሶርያዊው ፓትርያርክ በተነሣው ግጭት ምክንያት የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ሶርያዊው ፓትርያርክ እግናጢዮስ እንዲሾማቸው ጠይቀው ነበር ፓትርያርክ እግናጢዮስ ፈቃደኛ ቢሆኑም ይህ ሐሳብ በኢየሩሳሌም በተለያዩ የፖሊቲካ ምክንያቶች የተነሣ ተቃውሞ በማግኘቱ አልተሳካም፡፡

       እንዲሁም እ.አ.አ በ1323 ዓ.ም. ሁለት የፍራንሲስካን መነኮሳት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ መነኮሳት የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ሲፈጽሙ እንደተገኙ አስረድተዋል፡፡ ፍራንሲስካኑ መነኩሴ ኒኮሎ ዳ ፖጊቦንሲ እ.አ.አ በ1347 ዓ.ም. ከላይ እንደተገለጸው እትዮጵያውያን በቅድስት ማርያምና በቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደሶች በጎልጎታ ውስጥ የቅዳሴ ሥነ ስርዓት ይፈጽሙ እንደነበር ገልጾታል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ነገሥታት እንደ አጼ ካሌብ አጼ ይግበዓ ጽዮን አጼ ዘርዓያዕቆብ እና ሌሎችም ባበረከትዋቸው ስጦታዎች የኢትዮጵያ ገዳማት በኢየሩሳሌም ደምቀውና ከብረው ይታዩ ነበረ፡፡

       እንዲሁም በ14ኛው ክፍለ ዘመን የፍራንሲስካን መነኮሳት ሊኦናርዶ ፍሬስኮባልዲ እና ኦግዬር ዳንግሉር ኢትዮጵያዊያን በጎልጎታ ዓራት ቤተ መቅደሶች ይዘው እንደነበር መስክረዋል፡፡ እነዚህም፧ የእመቤታችንና የወንጌላዊው ዮሐንስ ቤተ መቅደስ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ የመጥምቁ ዮሐንስ ቤተ መቅደስ እና የማርያም መግደላዊት ቤተ መቅደስ ነበሩ፡፡ እነኚሁ አብያተ ክርስቲያናት በአርመኖችና በግሪኮች እጅ እንደተወረሱ በታሪክም አሁን የሚገኘው ተጨባጭ ሁኔታ ያስረዳል፡፡

      እ.አ.አ በ1479 ዓ.ም. ጀርመናዊው ሴቫልድ ራይተር በጽርሓ ጽዮን የሚገኘው ቦታ ከንጉሥ ዳዊት መቃብር አጠገብ የኢትዮጵያ ገዳም እንደነበር አስረድተዋል፡ ይህም ገዳም ተወርስዋል፡፡ በተጨማሪ አንጋፋው ኢጣልያዊ ታሪክ ጸሀፊ ቼሩሊ ኢትዮጵያዊያን የንግሥት ዕሌኒ ቤተ መቅደስና ኩራተ ርዕሱ ቤተ መቅደስ በጎልጎታና ጌታ በተወለደበት ቤተ ክርስቲያን በቤተልሔም ከተማ አንድ ቤተ መቅደስ እንደነበራቸው ይጠቅሳል፡ እነዚህም ከኢትዮጵያውያን እጅ ተነጥቀዋል፡፡

የደብረ ስልጣን ገዳም፡

      ደብረ ስልጣን ወይም ዴር ሱልጣን የሚባለው ገዳም ትርጉሙ “የንጉሡ ገዳም” ነው ይህ ገዳም አሁን ካሉት በኢትዮጵያውያን ይዞታ ከሚገኙት መካነ ቅዱሳት ታሪካዊ ቦታዎች አንዱና ለኢትዮጵያውያን መጠሪያና ለጥቁር ዓለም ምልክት ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ የዴር ሱልጣን ገዳማችን በጎልጎታ ከሚገኘው የንግሥት ዕሌኒ ቤተ መቅደስ በላይ የሚገኝ ሲሆን ከ9ኛው ምዕራፍ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይህ ቦታ ሦስት በሮች አሉት፡ ዋናው በር በስተ ሰሜን በኩል የሚገኝ ሲሆን ቁልፉ በግብጾች እጅ ይገኛል ይህንንም ቁልፍ በመያዛቸው በተለያዩ ጊዜያት በተለይም ወደ ጎልጎታ የሚወስደውን የምዕራቡን በር ቁልፍ በያዙበት ወቅት ሁለቱም በሮች በመቆለፍ በቦታቸው ላይ የሚገኙትን የኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ነፃነትን እና መብትን ለመግፈፍ የሞቱትን ጭምር ሬሳቸው እንዳይቀበር በማድረግ ከፍተኛ ግፍና በደል ፈጽመውባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው አጼ ምኒሊክ በደጃች መሸሻ አማካኝነት የምሥራቁን በር ያስከፈቱት፡ እንዲሁም በገዳሙ ወደ ሃያ የሚሆኑ የመነኮሳቱ መኖሪያ ቤቶች አብዘሃኛዎቹ በምሥራቁ በኩል ይገኛሉ እነኚህም አንድ ሰው እንክዋን የማያስተናግዱ ጠባብ ለጤንነት ጎጂ የሆኑ መስኮትና የአየር መግቢያ የሌላቸውና ከሀገሩ የአየር ፀባይ ጋር ለሕይወት አስጊ የሆኑናቸው በምዕራቡ በኩል ያለው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስም በመፈራረስ ላይ ይገኛል በኛ ይዞታ ላይ ከሚገኙት ከዴር ሱልጣን ገዳም ቤተ ክርስቲያን አንደኛው የአርባይቱ እንስሳት (መድኃኒ ዓለም) ቤተ መቅደስም ከቅዱስ ሚካኤል ቤተመቅድስ ጋር ተያይዞ የሚገኝ ነው፡፡

       እ.አ.አ በ1530 ዓ.ም. ዴኒስ ፓሶ የተባለው የፈረንሳይ ተሳላሚ የደብረ ስልጣን ገዳም በኢትዮጵያውያን ይዞታ እንደነበረ እንዲህ ሲል መስክሯል፡  “አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ሊሰዋበት የነበረውን ቦታ ሃበሾች የሚባሉት ጥቁር ሕዝቦት ቤተ መቅደሱን ይዘዋል በዚሁ ቦታ የአማረ የወይራ ዛፍ የሚገኝበት ሲሆን እስከ አሁን ድረስ የነበረውን ለዛ እንደያዘ ይገኛል ይህም ቦታ አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ለመስዋእትነት ያቀረበበት ነው ይህ ዛፍ እንደሚታወቀው በገዳማችን በዴር ሱልጣን የሚገኝ ነው::

       ቀጥሎም የፍራንሲስካኑ መነኮሴ ፍራንሼስኮ ዲ ቬርንዬሮ በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ እንዲህ ሲል ጻፈ “ኢትዮጵያውያን ከጎልጎታ አደባባይ ፊት ለፊት የሚገኘውን ቦታ እንደያዙ ባሉት ጠባብና ጨለማ ክፍሎች በባዶ መሬት ላይ ይታያሉ”: አለቃ ወልደ መድህን አረጋዊ በ1891 ዓ.ም. የሚከተለውን ታሪክ ጽፈዋል በ1774 ዓ.ም. እብራሂም ጀዋሂሪ የተባለው ግብጻዊ ከተከታዮቹ ጋር ኢትዮጵያዊያን በዴር ሱልጣን በእንግድነት እንደተቀበሉት በኋላም የቦታው ባለቤት እኔ ነኝ በማለት በኢትዮጵያውያኖቹ ላይ ጠብ በመፍጠር ከቦታቸው ላይ እንዳሰደዳቸው እንረዳለን፡፡

        እ…አ በ1838 ዓ.ም. ኢትዮጵያውያን መነኮሳትም በወረርሽኝ በሽታ በማለቃቸው ግብጾችና አርመኖች ይህንን ዕድል በመጠቀም የታሪክ መዛግብት በማቃጠል የነበሩትን መረጃዎች ሁሉ አብረው እንዲወድሙ አድርገዋል፡፡

       እ.አ.አ በ1820 ዓ.ም. ግብጾች ኃይል በመጠቀም አባ ገብረ ክርስቶስ የተባሉትን ኢትዮጵያዊ መነኩሴ በእጃቸው የነበሩትን የገዳሙን ቁልፎች ለመንጠቅ ችለዋል፡፡ ነገር ግን እ.አ.አ በ1850 ዓ.ም. ኢትዮጵያውያን በጊዜው ተጠናክረው ስለነበር የገዳሙን ቁልፎች ለማስመለስ ችለው ነበር፡፡ ሁኖም ግብጾች እ.አ.አ በ1862 መልሰው ኃይል በመጠቀም ቁልፎቹን በመለወጥ የቅዱስ ሚካኤልና የአርባይቱ እንስሳትም (መድኃኒዓለም) ቤተ መቅደሶች የመግቢያ በር ቁልፍ በመያዛቸው ከ1890 ዓ.ም. እስከ 1970 ዓ.ም. ለ80 ዓመታት በመቆለፋቸው ኢትዮጵያውያን መነኮሳት እንዳይጠቀሙባቸው አድርገዋል፡፡

      በ20ኛው ክፍለ ዘመን ይህ ጥያቄ ብዙ ውዝግብ በማስከተሉ የኢትዮጵያ ነገሥታት ከአጼ ምኒሊክ ጀምሮ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተውት ነበር በዚሁ ምክንያት አጼ ምኒሊክ የራሽያን ሽምግልና በመፈለግ ከራሽያ ጋር ባደረጉት የመልካም ግንኙነት ፍሬ እ.አ.አ በ1925 ዓ.ም. ባሮን ቦሪስ ኖልዴ የተባለው የራሻ የሕግ መምህር ባቀረቡት የሕግ አስተያየት የዴር ሱልጣን ገዳም የኢትዮጵያውያን መሆኑን አረጋግጠዋል፡ ይህም እ.አ.አ በ1852 ዓ.ም. የቱርኩ ሱልጣን አብደል ማጂድ በደነገጉት የስታቱስ ኮን ሕግ በመደገፍና ላለመሻር ነው፡፡ በየካቲት 1961 ዓ.ም. ይህንን ውሳኔ በመደገፍ የጆርዳን ፍርድ ቤት ለኢትዮጵያውያን ፍርድ ሰጠ፡፡ በዚህ ፍርድ መሠረት የቅዱስ ሚካኤልና የአርባይቱ እንስሳት (መድኃኒ ዓለም) ቤተ መቅደሶች የበር ቁልፍ ለኢትዮጵያውያን እንዲመለስ እንዲሁም በገዳሙ የሚገኘው ግብጻዊ መነኩሴ እንዲወጣ ተፈርዶ ነበር፡ ይህ ውሳኔ በጆርዳን ላይ ባስከተለው የፖሊቲካ ጫና በ40 ቀኑ እንዲለወጥ አደረገው፡፡

     በ1966 ዓ.ም. ጆርዳናዊው የኢየሩሳሌም ገዢ አሳይድ አንዋር አልኻጢብ ገዳሙ እንዲታደስ ውሃምኤሌክትሪክም እንዲገባ ካደረገ በኋላ ግብጾች ተቃውሞዋቸውን ለመግለጽ የፋሲካን ባዓል ኢትዮጵያውያን በሚያከብሩበት ሰዓት ድንጋይ አዘነቡባቸው፡: እ.አ.አ በ1970 ዓ.ም. እስራኤሎች የሁለቱም ቤተ መቅደሶች የበር ቁልፍ ቀይረው ለኢትዮጵያውያን አስረከቡ በተጨማሪም በወቅቱ የነበሩትን የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ለዚህ ቁልፍ መለወጥ ሙሉ ኃላፊነት መውሰዳቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ አስፈርመው ተቀበሏቸው፡፡ ይህንን አስመልክቶ በወቅቱ የነበረው የግብጽ ሊቀ ጳጳስ ወደ እስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በማቅረብ በመጋቢት 1971 ዓ.ም. የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስታቱስ ኮ ከተጣዕ ሁኔታው ወደነበረበት እንዲመለስ ውሳኔ ሰጠበት ሆኖም ግን የእስራኤል መንግሥት ጉዳዩ በሚኒስትሮች ኮሚቴ እንዲጠና መረጠ ኮሚቴው ውሳኔ ላይ እስኪደርስ ቁልፎቹ በኢትዮጵያውያን እጅ እንዲቆዩ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ ከዛን ወቅት ጀምሮ ጉዳዩ ባለመንቀሳቀሱ በቦታው የሚገኙት ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ከዕለት ወደ ዕለት ችግራቸው እየተባባዕ በመምጣቱ የመኖሪያ ቤቶቻቸው እንዲሁም በገዳሙ የሚገኘው የመጸዳጃ ቦታ ለእነርሱም ለጎብዮችም ጤንንት ጠንቅ በመሆኑ ቤተ መቅድሶቹም በመፈራረሳቸው አገልጋይ ካህናቶቹ እና ምዕመናኑ የሚረግፈውን አቧራ በዕድሳት ለማስወገድ ባለመቻላቸው በከፍተኛ ጉዳት ላይ ይገኛሉ፡፡

     በቅርቡ ይህንን ጥያቄ ለመከታተልና ለመፍታት በዓለምአቀፋዊ ቅንብር አንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ በሚያዝያ 98 በኢየሩሳሌም ከተማ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄዶ ነበር፡፡

ሌላ አብይ ንብረቶች፡

ከዚህ ሌላ በቅድሰት ሀገር ነገሥታቱና መኳንንቱ ያበረከትዋቸው ቦታዎች ይገኛሉ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው

  1. ደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት፡ እ.አ.አ በ1884 ዓ.ም. በአጼ ዮሐንስ 4ኛ ዘመነ መንግሥት ስራው ተጀምሮ በ1893 ዓ.ም. በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መነግሥት ተፈጸመ።
  2. መንበረ ሊቀ ጵጵስና፡ በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የተገዛ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የገዳማቱ ጽፈት ቤት እና የቅዱስ ፊሊጶስ ቤተ መቅደስ የሚገኝበት በተጨማሪም የሊቀ ጳጳሱ መኖሪያ ቤትም ነው።
  3. ኢያሪኮ ቤተ አማረች በ1920ዎች ወ/ሮ አማረች ዋለሉ ያበረከቱት ቦታ የኢያሪኮ ገዳም ተብሎ የሚጠራ በአሁኑ ጊዜ የቅድስት ሥላሴ መቃኞ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ይኸውም በአቡነ ታዴዎስ የተሰራ የግል ቤታቸው የነበረ ነው በዚሁ ቦታ የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ለማሰራት መሠረቱ ተጥሏል።
  4. ቅድስት ሥላሴ፡ በግርማዊት እቴጌ መነን በ1933 ዓ.ም. በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የተሰራ ሲሆን በቅድስት ሥላሴ የተሰየመ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ይህ ገዳም ከስድስቱ ቀን የእስራኤሎችና የአረቦች ጦርነት ወዲህ የጦር ክልል በመሆኑ በቦታችን ላይ ለመገልገል አልተቻለም፡፡
  5. ቤተ ዓላዛር ምስካበ ቅዱሳን ተብሎ ዛሬ የሚታወቀው ቦታ በ1950ዎቹ በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የተገዛ ሲሆን በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ጊዜ ገዳሙ ተመሥርቶና ተሰርቶ በውስጡም በአቡነ ተክለ ሃይማኖት የተሰየመ ታቦት ይገኝበታል እንዲሁም በቦታው የአረጋውያን እናቶችና አባቶች መጦሪያ ቤት በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ጊዜ በ300,000 ዶላር የተሠራ ይገኛል፡፡
  6. የቤተልሔም ገዳም: የራስ ካሣ ቤት የነበረ ሲሆን የኢየሩሳሌም ድርጅት መሥራች በአቶ መኮንን ዘውዴ አነስተኛ ቤት ተገዝቶ በ1990 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ኣትናቴዎስ ጊዜ ደብረ ሰላም ኢየሱስ ቤተ መቅደስ ታንጾ ይገኛል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ተጨማሪ ከገዳሙ ጋር የተያያዘ ቤት በብፁዕ አቡነ ገሪማ ዘመነ ክህነት በ300,000 የአሜሪካ ዶላር ተገዝቷል፡፡
  7. ተጨማሪ ቤቶች ያበረhቱ አጼ ምኒሊክ እቴጌ ጣይቱ ንግሥት ዘውዲቱ፤ አባ ወልደ ገብርኤል አፈንጉሥ ነሲቡ፤ ወ/ሮ ደስታ እና እህታቸው እማሆይ ወለተ ተክለ ሃይማኖት፤ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ራስ ወልደ መሸሻ ወ/ሮ በየነች ገብሬ ናቸው።

ማጠቃለያ፡

          የዴር ሱልጣን ጥያቄ ከሀገር ጉዳይ አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የታሪክ ምልክት እናም መመኪያ የመሆኑን ያህል የተሰጠው ትኩረት እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ አሳዛኝ ነው፡፡ በጉልህ የሚታዩት ችግሮች በሦስት መክፈል ይቻላል 1) በውስጥም በውጭም ጉዳዩን የሚከታተሉ የምዕመናን ድርጅቶች ባለመኖር 2) በቂ ግንዛቤ እጥረት 3) የኢየሩሳሌምን ገዳም ውስጣዊ ችግሮች፡፡

በዚህ መንፈስ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች

1ኛ የምዕመናን ተሳትፎ፡

ሀ) የኢየሩሳሌም ገዳም የተለያዩ ችግሮቹን እንዲፈታ የምዕመናን ተሳትፎ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ምዕመናን ሁሉ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል ይህ ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ዓለምhቀፋዊ የምዕመናን ድርጅት ተዋቅሮ ለዚህ ዓላማ ቅድሚያ ሰጥቶ ከኢየሩሳሌም ገዳም ጋር በመሥራትና ሀሳቦች በመለዋወጥ አስቸኳይ መፍትሔዎች መሰንዘር፡ በዚህ መንፈስ በነሐሴ 98 በተካሄደው የኢየሩሳሌም ማኅበረ መነኮሳት ጉባዔ ከላይ የተጠቀሰው ኮሚቴ ተስፋፍቶ ከማኅበረ መነኮሳቱም ውስጥ ተወካዮች ተገኝተውበት ሥራውን እንዲያከናውን ጥይቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ለ) በኢየሩሳሌም ከተማ የተለያዩ ጠቃሚ ፕሮጄክቶች መጀመር ለምሳሌ አነስተኛ ሆቴል ቤት መሥራት የእነዚህ ፕሮጄክቶች ዓላማ 1) ገዳሙ ራሱን እንዲችል ማድረግ 2) ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክ ማውረስ 3) ከአገሩ ነዋሪ ሕዝብ ጋር ጥሩ ግንኙነት ማዳበር፡፡

2ኛ ግንዛቤ ለማዳበር፡

ሀ) የዴር ሱልጣንን ጉዳይና የአባቶችንና የእናቶችን ስቃይና በደል በተለያዩ ዘመናዊ የመገናኛ ብዙኃን በመጠቀም በሰፊው ማሳወቅ፡፡

ለ) የታሪክና የሕግ ተማሪዎች በዴር ሱልጣን ጥያቄ ጠቃሚ ጥናቶችን በማድረግና ተግባራዊ መፍትሔዎች በመሰንዘር ለሚመለከታቸው አካሎች አቅርበው የተሻለ ግንዛቤ ማስገኘት፡፡

መ) በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም አንዲት ጥቅር ቤተ ክርስቲያን ብቻ በመኖርዋ የዴር ሱልጣንን ጥያቄ ለጥቁር ወንድሞቻችን በተለይ አሜሪካ ላሉት ላማስጨበጥ ከፍተኛ የሎቢ ጥረት ማድረግ፡፡

ረ) ይህ ቦታ የኢትዮጵያውያንና የጥቁሮች ምልክት እንደመሆኑ መጠን የተደራጀ ሕዝብ መጥቶ እንዲመለከተውና እንዲጎበኘው ማድረግ፡፡

3ኛ የገዳሙ ውስጣዊ ችግሮች፡

የገዳሙ ዋና ውስጣዊ ችግር በአንደኛ ደረጃ የዘመናዊ አሰራርና አስተዳደር ባህል አለመኖሩ ሲሆን ይህ እጥረት ሌላ ልዩ ልዩ ችግሮች አስከትሏል ለምሳሌ የገዳሙ ቤቶች ተከራዮች በሕግ ተገቢ የሆኑትን ግብሮች ባለመክፈል አንድ አንድ ቤቶቹ በእዳ ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡ የዚህ ችግር ዋና መነሻ የሆነው በገዳሙ ውስጥ በዘመናዊ ትምህርት የተሰማራና የሀገሩን ባህልና ቋንቋ የሚችል ሰው በመጥፈቱ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድ፤

ሀ) የገዳሙ አባቶች ከምዕመናን ውስጥ ባለሞያ የሆኑትን የመቅጠር አስፈላጊነት ማስረዳት፡፡

ለ) ከአባቶችና ከእናቶች ወጣት የሆኑትንና ችሎታ ያላቸውን ዘመናዊ የትምህርት ዕድል ማስገኘት፡፡

የዚህ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ የኢየሩሳሌምን ገዳም ታሪካዊነትና አስፈላጊነት በመረዳት ለዚህ ጉዳይ ሰፊ አጄንዳ በመያዙ ከልብ ላመሰግነው እወዳለሁ።

ዳንኤል እስጢፋኖስ ዓለሙ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top